Youth

የሰንበት ት/ቤት ታሪክ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ

በኢትዮጵያ ኦርቶክስ ተዋህዶ ቤተክርስተያን ታሪክ የወጣቶች ሰንበት ት/ቤት ማቋቋም የተጀመረው ከ1936 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ የኸውም ከብዙ ዓመታት በፊት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሃይማኖት ትምህርት ይከታተሉ የነበሩ ወጣቶች “የሥላሴ ማህበር” ተብሎ የሚጠራ አንድ ማህበር መሠረቱ፣ ይህ ማህበር ለወንዶች ብቻ የተቋቋመ ነበር ይሁንና ከጥቂት ዓመታት በኋላ የካቴድራሉ አስተዳደር ወጣት ልጃገረዶችም የራሳቸውን ማህበር መመሥረት እንዳለባቸው አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘው ለጸሎትና ለአምልኮ ወደ ካቴድራሉ የሚመጡ ልጃገረዶችን ሰብስቦ እነርሱም የራሳቸውን ማህበር እንዲያቋቁሙ አበረታታቸው በመሆኑም “ማህበረ ክርስቶስ” በሚል መጠሪያ የሚታወቅ ማህበር መሠረቱ፡፡

የእነዚህ ማህበር አባላት የተሻለ የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ትምህርት ማግኘት ሲጀምሩ የቤተክርስቲያንን ትምህርት እየተማሩና እያወቁ በመምጣታቸው በተለይም ልጃገረዶች የቤተክርስቲያንን ዜማ በማጥናት በቤ/ክ ውስጥ ከቁርባን በኋላ መዘመር ጀመሩ፡፡ ይህም እንደ አዲስ ክስተት ታይቶ በካህናቱና በምእመናኑ ዘንድ የሚወደድ ሆኖ ተገኘ የእነዚህ ማህበራት ዓላማቸውም የሚከተሉት ነበሩ፡-

  1. የክርስትና ሃማኖትን መሰረታዊ ዓላማዎች መማርና ማስተባበር ፣

  2. ሰብአዊ ተግባራትን ማካሄድ፣

  3. የክርስቲያንን ብሔራዊ ባህል መጠበቅ፣

  4. ወጣት ልጃገረዶች ያለፍርሃት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉና ለህበረተሰቡ አገልግሎት የሚስፈልገውን የሥራ አመራር ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ናቸው፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው በቅዳሴ ጊዜ የወጣት ልጃገረዶች ተሰጥዎ መቀበልና ከቅዳሴም በኋላ ልዩ ልዩ ጣዕመ ዜማዎችን ማስማታቸው እንደ አዲስ ነገር በመታየቱ ተግባሩ በሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት ወጣቶች ቀጥሎ ተስፋፍቷል፡፡ የምስካየ ኅዙናን ቤተክርስቲያን ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በሚሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት የተፈሪ መኮንን እና የእቴጌ መነን ት/ቤት ተማሪዎችን በብዛት መሳብ በመቻሉ በየሳምንቱ እሑድ ተማሪዎች በብዛት ወደ ቤ/ክ እየመጡ በመንፈሳዊ አገልግሎት ተሳታፊ ከሆኑ በኋላ ብዙዎች በቤ/ክ እንዳንድ ሥራዎች በፈቃደኝነት መሳተፍ ጀመሩ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተማሪዎችና በገዳሙ መካከል አንድነትን መፍጠር የሚችልና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚሰጥበት ሰንበት ት/ቤት እንዲቋቋም ወጣቶቹ በመጠየቃቸው  “ተምሮ ማሰተማር” የተባለው ታዋቂው ሰንበት ት/ቤት በ1939 ዓ.ም ተመሠረተ፡፡ የተምሮ ማሰተማር ማህበር ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ለማህበሩ አባላትና ለህብረተሰቡ አስፈላጊ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ ከዚያ በመቀጠል በ1942 ዓ.ም የተቋቋመው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሲሆን የወንጌል መልዕክተኞችና የእሑድ ት/ቤት ማህበር ተመሠረተ፣ በዚሁ ጊዜም ነበር የአሥመራው ማህበረ ሐዋርያት ፍሬ ሃይማኖት ማህበር የተቋቋመው፡፡

ሥነ ፍጥረት

ሥነ ፍጥረት ማለት ምን ማለት ነው?

ሥነ ፍጥረት የሚለው ቃሉ የግእዝ ሲሆን ሥነ የሚለው ቃል “ሠነየ” አማረ ውብ ሆነ ማለት ነው፡፡ ፍጥረት የሚለው ደግሞ “ፈጠረ” አስገኘ፥ ካለመኖር ወደ መኖር አመጣ ማለት ነው፡፡ ሥነ ፍጥረት ማለት ያማረ ፥ ውብ የሆነ ፥ የተደላደለ ፥ መልካም የሆነ ፍጥረት ማለት ነው፡፡ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ እነሆ እጅግ መልካም ነበረ” ተብሎ እንደተጻፈ (ዘፍ 1፥23 ፤ 1፥31)

እግዚአብሔር ዓለም ሳይፈጠር አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠቀልለው ሦስትነቱ አንድነቱን ሳይከፍለው እንደዛሬ ሁሉ በአንድነት በሦስትነት ሲሠለስ ሲቀደስ ይኖር ነበር ፍጥረት ሳይኖር ማን ያመሰግነው ነበር ቢሉ ምስጋና የባሕርዩ ስለሆነ አንድም ምስጉን ባሕርይ በቅድምና ስለነበረ ለሦስት ዓላማዎችም ፍጥረታትን ፈጠረ ከፍጥረታት መካከል ሰውና መላእክትን ስሙን ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ የተፈጠሩ ሲሆን የተቀሩት ፍጥረታት ግን ለአንክሮ ለተዘክሮ ለምግበ ሥጋ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ (መዝ 148፥1-3፣ ራዕ4፥11፣ ሐዋ 14፥17፣ ሮሜ 1፥21) ይኸውም ስለአምስት ነገር ፈጥጥታል ከሀሊነቱን ባዕልነቱ ርኩብነቱ ዘኢይትረከብነቱ ራትዕነቱን ለመግለጥ ነው፡፡ ከሀሊነቱ ይህንን ዓለም እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ መፍጠሩ በኋላም እምኀበ ቦ ኀበ አልቦ ማሳለፉ ባዕልነቱ ዛሬ ባለጠጋ ሀሉን ጠርቶ ሲያበላ ሲያጠጣ ለሁሉ የሚያስፈልገውን እንደሚጋብዝ ጌታም ሰውን ፈጥሮ የሚያስፈልገውን ለመላእክትም እንዲሁ የሚያስፈልጋቸውን አድርጎልና ርኩብነቱ በሥነ ፍጥረት ይገለጣልና ዘኢይትረከብነቱ ባሕርዩ አይመረመረምና ራትዕነቱ ዲያቢሎስ ቢስት እናዳይመረስ አውቆ ቦታውን ለአዳም ሰጥቶታል አዳም ቢስት እንዲመለስ አውቆ ቦታውን ለመላእክት አስጠብቆለታል፡፡(ዘፍ. 3÷24)